Tuesday, May 13, 2014

የዞን ዘጠኝ ብሎግ ጸህፊያን የታሰሩበት ምክንያት፤ እኔ እንደደረስኩበት...

የዞን ዘጠኝ ብሎግ ጸህፊያን የታሰሩበት ምክንያት፤ እኔ እንደደረስኩበት...
እንዚህ ልጆች ከታሰሩ በኋላ "ሆደ ሰፊው" መንግስታችን ለምን አሰራቸው ብዬ አጥብቄ ስመራመር ቆይቻለሁ። በመጨረሻም እነሆ የምርምሬ ውጤት በሁለት አንቀጽ እንደሚከተለው ይቀርባል።
ዘጠኝ ጓደኛማቾች በአንድ መድረክ ላይ አብረው ለመጻፍ ተደራጁ፤ የሚጸፉበትን መድረክም ዞን ዘጠኝ በለው ሰየሙት። በዞን ዘጠኝ የጡመራ መድረካቸው ለእስር የሚያበቃ ክፉ ነገር አንዳችም እንዳልተናገሩ ከምላሴ ፀጉር በዬ ምዬ እኔ እማኝ እሆናለሁ። እገረ መንገዴንም ሀገራችን ሰዎችን ለምን ጻፋችሁ ብላ እንደማታሰርም ታማኙን ኢቲቪን ጠቅሼ እመሰከራለሁ... መቼም ዘመኑ ታማሚ እና ታማኝ የተምታታበት ዘመን ሆኗል!
እናም እንደምርምሬ ከሆነ ዞን ዘጠኞች የታሰሩት ስለጻፉ አይደለም። ዘጠኝ ሆነው ከመንግስት እውቅና ውጪ የጠበቀ ጓደኝነት ሰለመሰረቱ ነው። መንግስታችን በአሁኑ ጊዜ ዜጎች በ አንድ ለአምስት አደረጃጀት እያደራጀ ባለበት ወቅት እነርሱ ከዚህ አደረጃጀት ውጪ ዘጠኝ ሆነው መደራጀታቸው፤ ለመታሰራቸው ዋና ምክነያት ሆኗል። እነዚህ ወጣቶች አንድ ለአምስት አደረጃጀቱ ካለተመቻቸው በመንግስት እውቀና ባለውን ጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጀተው ያሻቸውን ማደረግ ሲቸሉ እነርሱ አንድ ለአምስትም፤ አነስተኛ እና ጥቃቅንም ሳይሆኑ ዞን ዘጠኝ በሚል ስም ልማታዊ መሆኑ በመንግስት ያልተረጋገጠለት ጓደኝነት መመስረታቸው ታላቅ ጥፋት ሆኖ ተገኝቷል።
መደምደሚያ
ከንግዲህ ኢህአዴግዬ በህይወት ሳለች፤ የሰፈር ወዳጅነትም ሆነ የትምህርት ቤት ጓደኝነት ቁጥሩ ያነሰ እነደሆነ፤ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ቁጥሩ የበዛ ከሆነ ደግሞ በአነስተኛ እና ጥቃቅን መታቀፍ ይገባዋል። ያ ሳይሆን ቢቀር ግን ስብስቡም ሆነ ማህበሩ ቤቱ ቃሊይሆናል!
ምስኪን ኢህአዴግዬ ስንቱን ፈርታ፤ ስንቱንስ አቅፋ ትችለዋለች! እንልና... (በቅንፍም፤ ያገኙትን ሁሉ ልቀፍ ማለት ምስኪነነት ሳይሆን አመንዝራነት ነው በሎ ማሽሟጠጥ ይቻላል!) ብለን ቅንፋችንን ዘግተን ሃሳባችንንም እንቋጫለን!

Source -Abe tokichaw

No comments:

Post a Comment