Monday, June 2, 2014

ማዕከላዊ ማጎሪያ ሄጀ ነበር፡፡

ትላንት በነበፍቄ የፍርድ ሂደት ሊታደም ሄዶ መታወቂያው ተውሰዶ ሰኞ ማእከላዊ ቅረብ የተባለው ጋዜጠኛ በላይ ማናየ ዛሬ ሄዶ የገጠመውን ያወጋናል
ልታሸብሩኝ አትሞክሩ!
ማዕከላዊ ማጎሪያ ሄጀ ነበር፡፡
ዕሁድ በአራዳ ምድብ ችሎት የዞን 9 ጦማሪዎችን የፍርድ ውሎ ለመከታተል በቦታው ነበርኩ፡፡ ችሎቱ በዝግ ታዬ፤ ምንም አላልንም፡፡ ከውጭ ጠብቀን የፍርድ ውሳኔውን ለመስማት ስንጓጓ ምንም ሳንሰማ የፍርድ ቤቱን ግቢ ለቅቀን እንድንወጣ ታዘዝንለ፡፡ ወጣን፡፡ በዚህ ሳያበቃ ደግሞ ከግቢው ውጭም እንድንርቅ አዘዙ፡፡ ይህኔ ወደፍርድ ቤቱ የሄድነው የፍርዱን ውሳኔ ለመስማትና ወዳጆቻችንን ለማየት እንደሆነ ገልጬ ‹ለምን እንወጣለን?› ብዬ በመጠየቄ ከሰው ለይተው አገቱኝ፡፡
እገታው ለአጭር ጊዜ የቆየ ቢሆንም በጣም ዘግናኝ ስድቦችንና ጥያቄዎችን ሰንዝረውብኛል፡፡ መጠየቄ ወንጀል ሆኖባቸው ያለ የሌለ ማስፈራሪያና ዛቻ አውርደውብኛል፡፡ በዚህም ሳያበቁ መታወቂያየንና የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር የያዘ ካርዴን ነጥቀውኛል፡፡ ለምን ብዬ ስጠይቅ ምላሽ አልነበራቸውም፡፡ ከዚያ ይልቅ ዛሬ ሰኞ ማዕከላዊ ማጎሪያ ድረስ እንድቀርብ ትዕዛዝ አወረዱ፡፡
እናም ዛሬ ማዕከላዊ ሄጄ ነበር፡፡ በቅጡ የሚናገርም የሚያዳምጥም የለም፡፡ መታወቂያየን እንዲመልሱልኝ ለመጠየቅ እንኳ እድሉን ላገኝ አልቻልኩም፡፡ በር ላይ ያለው ሰው አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ ቀረበ፡፡ አብሮኝ የነበረው ጓደኛዬ ብርሃኑ በጥሞና ሊያስረዳው ሞከረ፤ መስሚያም የለው!
ከግቢው ዞር እንድንል አዘዘ፡፡ አሁንም ግን ልናስረዳው ሞከርን፡፡
‹‹መታወቂያህን አልወሰድንም….ማን ነው የወሰደብህ…..የወሰዱብህን ሰዎች ስም ጥራ›› አለኝ፡፡
ስማቸውን እንዴት ላውቅ እችላለሁ? ማንስ እንድጠይቅ ፋታ ሰጠኝ?
‹‹ነገ መጥተህ ሪፖርት አድርግ፤ መታወቂያህ ከእኛ ጋር ይቆያል›› ነበር ያሉት ትናንት መታወቂያየን ሲነጥቁኝ፡፡
‹‹የት…ማን ብዬ ልጠይቅ?››
‹‹ቦቃ ማዕከላዊ ዙም ብለህ ና አልኩህ፤ ምን ቾገር ትፈጥራለህ!›› ሲቪል የለበሰ ኮሳሳ ሰውዬ አንቧረቀብኝ፡፡
እና አሁንም እያደነጋገሩ ሊያሸብሩ ነው የሚሞክሩት፡፡ ስርዓቱን አውቀዋለሁና አዲስ ነገር አልሆነብኝም፡፡ ደስ ባላቸው ጊዜ ይጠራሉ፤ ያስራሉ፤ ይገድላሉ…እነሱ ብቻ አዋቂ፣ እነሱ ብቻ ተናጋሪ ናቸው፡፡
ደግሞ እኮ ብዙ ጊዜ እንደ ለማዳ ውሻ ከኃላ ከኋላዬ የሚከተሉኝ ሰዎቻችሁንም ተላምጃቸዋለሁ፡፡ ስለእኔ መረጃ ለመሰብሰብ እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ እናንተ የምትከተሉኝ ከማን ከማን ጋር እንደምገናኝ ለማወቅ ነው፡፡ የመረጃ ምንጮቼን ለማስፈራራት ነው፡፡ ይህን ደግሞ ራሳችሁም ነግራችሁኛል፡፡
እናንት የማዕከላዊ ሰዎች…መታወቂያየን ብትመልሱልኝ ደስ ይለኛል፤ ልማጸናችሁ ግን አልፈልግም፡፡ እናንተ እንደሆን ህግን አትፈሩም፤ አታከብሩም! ግን ግን ልታሸብሩኝ አትሞክሩ፤ ስራዬን ጠንቅቄ አውቃለሁና አልሸበርም! እኔ ሰላማዊ ሰው ነኝ፡፡
እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው፣ መቼም ቢሆን ከምወደው ስራዬ ፈቅ እንደማልል ነው!
ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም!

No comments:

Post a Comment